በከተሞች አካባቢ ልጅ ስለመውለድ ሲነሳ ዳይፐር ቀድሞ ይነሳል። ለወላጆች ከወተትና ሌሎች ግብዓቶች የበለጠ እጅግ በጣም አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል።
በቀድሞው ዘመን እናቶች ነጠላንና ጋቢ ጨርቅን በአነስተኛ መጠን በመቆራረጥና በማጠፍ ለሽንት መቀበያነት ያውሉ ነበር። በገጠሩ የአገራችን ክፍል እስከ አሁን የሚገለገሉት በዚሁ በቤት ውስጥ በሚዘጋጅ ጨርቅ ነው። በዓለማችን የሽንት መቀበያ ጨርቅ (ዳይፐር ) መመረት የጀመረው በ1940ዎቹ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት በጣም በተራቀቀ መልኩ ልዩ ልዩ ዓይነት ዳይፐሮች ተመርተው ለተጠቃሚ እየቀረቡ ነው። ምርቱም የቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ሆኗል።
የዳይፐር ዓይነቶች
በጣም በርካታ የዳይፐር ምርት ዓይነቶች አሉ። ክፍፍሉ የሚሰሩበትን ቁስ፣ አጠቃቀማቸውን እና ሌሎች ባህርያትን መሰረት በማድረግ ነው። በዋናነት ግን በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ።
ሀ. የጥጥ ዳይፐር እና
ለ. ተጠቅሞ የሚጣል (Disposable Diaper)
የጥጥ ዳይፐር ስሙ እንደሚነገረን ከጥጥና መሰል ግብዓቶች የሚሰራ ሲሆን ከተጠቀምን በኋላ እያጠብን መላልሰን መጠቀም የሚያስችለን ምርት ነው። በዚህም ወጪ ቆጣቢ፣ ብክለት ቀናሽና ለህፃናት ቆዳ ተስማሚ እንደሆነ ይነገራል።
ሁለተኛው ዓይነት አንዴ ተጠቀመን የምንጥለው ዳይፐር ሲሆን ለአጠቃቀም የተመቸ፣ የክብደቱን 15 እጥፍ ያህል ፈሳሽ መጦ የማስቀረት አቅም አለው። ቶሎ ቶሎ መቀየርን በአንፃራዊነት ያስቀራል ማለት ነው። በአሰራሩ ብዙ ፈሳሽ መጦ እንዲያስቀር ያስቻለው ከፍተኛ መጣጭ ቁስ (Super Absorbent Polymer-SAP) የተባለ ቁስ በውስጠኛው ክፍል ስላለው ነው።